ሱስ አምጪ ዕፆችና የአልኮል አጠቃቀማችን ማህበራዊ ቀውስ እያስከተለ እንደሆነ ተገለፀ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የዓመቱን ስድስተኛ የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረክ መጋቢት 27/2010 ዓ.ም ሱስ አምጪ ዕፆችና የአልኮል አጠቃቀም በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ …

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የዓመቱን ስድስተኛ የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረክ መጋቢት 27/2010 ዓ.ም ሱስ አምጪ ዕፆችና የአልኮል አጠቃቀም በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ አካሄደ፡፡

ሳንሳዊ ገለፃውን ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በህክምና ትምህርት ቤት የሳይካትሪ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ሰለሞን ተፈራ ናቸው፡፡ ዶ/ር ሰለሞን ሱስ የሚያስይዙ ዕፆች፣ መድሀኒቶችና የአልኮል ይዘት ያላቸው መጠጦችን መጠቀምን ተከትሎ የሚከሰቱ የጤና፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች የሰው ልጅ የሚቸገርባቸው አለም አቀፋዊና አገር አቀፍ ጉዳዮች እየሆኑ መምጣታቸው ገልጸዋል፡፡

ሱስ አምጪ ዕፆችና አልኮል አጠቃቀማችን ተደጋጋሚነት (ስር-ሰደድ)፣ ውስጣዊ ግፊት፤ አዘውትሮ ማሰብ፤ ቁጥጥር ማጣት፤ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት፤ ጤና ማህበራዊ ቀውስ መከሰት፤ ተጠቃሚው የሚወስደውን መጠንና መቼ  እንደሚወስድ ለመወሰን መቸገር፤ የጤና ችግር እንደሚያባብስ እንዳለ እያወቁ መጠቀም፤ የሚጠቀሙትን ሱስ አስያዥ ነገር በመጠንም ሆነ በጥንካሬ በየጊዜው መጨመር፤ ሳይጠቀሙ ሲቀሩ ስነ-ልቦናዊም ሆነ አላካዊ ችግሮች መከሰት እና የመሳሰሉት መገለጫዎች የሚታይበት ግለሰብ በሱስ ለመጠመዱ መሠረታዊ ጥቁምታዎች ናቸው ይላሉ ዶ/ር ሰለሞን፡፡

2

በአልኮል አጠቃቀም ረገድ እ.ኤ.አ በ2000  የኢትዮጵያ ዓመታዊ የቢራ ምርት መጠን 100 ሚሊዮን ሊትር አካባቢ የነበረ ቢሆንም፣ በየአመቱ ከ15-20% እያደገ አሁን ዓመታዊ ምርቱ 1.2 ቢሊዮን ሊትር ደርያሉት የገለፃው አቅራቢ፤ በአማካይ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ 12 ሊትር ቢራ በዓመት የነፍስ-ወከፍ ድርሻ ይኖረዋል እንደማለት ነው፡፡ አክለውም በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2015 ከ10ሺ በላይ ተሳታፊዎች ላይ ተመስርቶ በተደረገ አገር-አቀፍ ጥናት መሠረት በአማካይ 15.8 ከመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ጫት ቃሚ ሲሆን፤ ከቅርብ ዓመታ ወዲህ በርካታ ቁትር ያለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪ በጫት ሱስ አዙሪት ውስጥ እንደወደቀ አቅራቢው ጥናቶችን ጠቅሰው የችግሩን ስፋት አሳይተዋል፡፡ የትንባሆ አጠቃቀምን አስመልክቶም ባጠቃላይ አመታዊ የሲጋራ ፍጆታው ከ10 ቢሊዮን የሲጋራ ቅንጣቶች (ሲጋራ በፍሬ) በላይ እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡

እንደ አጠቃላይ እነዚህ ችግሮች ዘላቂና ሁነኛ እልባት ካላገኙ ለወንጀል መስፋፋት፣ ለኢኮኖሚ ድቀት፣ ለማህበራዊ እሴት መላሸቅ፣ ለቤተሰብ መበተን፣ ለጎዳና ተዳዳሪነት እና ባስ ሲልም ለሀገር ውድቀት መንስኤ ከመሆን የሚያግዳቸው አይኖርም፡፡

ውጤታማ የመከላከያ መንገዶች

በዕለቱ ሳይንሳዊ ገለፃ፣ የገለፃው አቅራቢ ዶ/ር ሰለሞን እና ተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት በማድረግ የሚከተሉትን የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ጠቁመዋል፡-

1

  • በአልኮል መጠጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ወጣቶች የአልኮል መጠጥ የሚጀምሩበትን ዕድሜ ማዘግየት፤
  • አምራች ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ግብር በመጣል የምርት መጠናቸውን እንዲቀንሱ ጫና ማሳደር፤
  • በሱስ አምጪ ዕፆች  ምርት፣ ህገ-ወጥ ዝውውርና ሽያጭን ለማስወገድ ጠንካራ ግብረ-ኃይል ማደራጀት፤
  • የዕድሜ ገደቦች በአግባቡ እንዲተገበሩ ግፊት ማድረግ፤
  • ልቅ የሆነ የአልኮል ማስታወቂያና የመገናኛ ብዙሃን ግዴለሽነትን በህግ መቆጣጠር፤
  • በአልኮል ዘርፍ የሚመጣውን ከፍተኛ የውጪ መዋዕለ-ንዋይ በሌላ የልማት ዘርፍ እንዲሠማራ ማበረታታት፤ ማትጋት፤
  • አርሶ አደሩን ከጫት ምርት ወደሌላ የተሻለ ኤኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ወዳላቸው ሰብሎች/ተክሎች ማሸጋገርና ማገዝ፤
  • አሁን ያለውን የማስታወቂያ አዋጅ እንደገና መፈተሽ፤
  • ሁሉን-አቀፍ ሳይንሳዊ ጥናቶችን በማስጠናት ስርጭቱንና ጉዳቱን በመረጃ አስደግፎ ለፖሊሲ አውጪዎች ማቅረብ፤ እና
  • በፌደራል፣ በክልልና በታችኛው መዋቅር የተዘረጉ የፍትህ ተቋማት ከአስፈፃሚ አካላት ጋር የተመጋገበና ያልተቋረጠ ሥራ መሥራት ናቸው፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *