ለሥነ ጥበባት እድገት የሂስ ባህልን ለማጎልበት ያቀደ ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት አስተዋጽዖ ያበረከቱ ደራሲያን አበርክቶ ላይ ያተኮረ የሂስ መድረክ ተካሄደ


“ኪነ ጥበብብን ለማሳደግ ኪነ ሂስን ባህል እናድርግ” በሚል መሪ ቃል የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ባዘጋጀው የውይይት መርሐ ግብር ላይ ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ባሻገር ለአማርኛ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍ ድርሰት ዕድገት ባለውለታ በሆኑ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ላይ ያተኮረ የሂስ መድረክ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል ቅጥር ግቢ አካሂዷል።
የሂስ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የቢሮው የኪነ ጥበብብ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሠርጸ ፍሬስብሐት ‘‘ሂስ ምስጋና፣ ነቀፋ፣ወይም ትችት ሳይሆን በአንድ ደራሲ እና ተደራሲ ሥራ መካከል የሚሰጥ ብያኔ፣ትንተ እና ሙያዊ ትርጉም የማዋለድ ጥበብ ነው’’ ብለዋል።
በሀገራች በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ሂሳዊ ፍተሻ እንደሚደረግባቸው የገለጹት አቶ ሠርጸ በሥነ ጥበባት ሥራዎች ላይ የሚደረግ የሂስ ልማድን በመደበኛነት ወደ ተግባር ከማሰገባት አንጻር ክፍተት እንዳለ ገልጸዋል።


በኪነ ጥበበ ሥራዎች ላይ ሙያዊ ሂስና ዳሰሳ ማድረግ ኪነ ጥበቡን እንደሚያሳድገው ገልጸው ቢሮው ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በዘርፉ ላይ የሚያተኩሩ ኪነ ጥበብባዊ የሂስ መድረክ ያካሄደ ሲሆን ከነዚኽም ሁለቱን በሳይንስ አካዳሚ ግቢ ማድረጉን አውስተዋል።
አያይዘውም የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የሥነ ጥበባት ዘርፎችን በሳይንሳዊ መንገድ ለማሳደግ እያደረገ ላለውን ጥረት አካዳሚውን አመስግነዋል።
ለተሳፊዎች የእንኳን ደህና መጣችኹ መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ አካዳሚው በሥነ ጥበባት ማዕከሉ በኩል ሥነ ጥበባትን በሳይንሳዊ መንገድ ለማሳደግና ተደራሽ ለማድረግ በየ አሠራ አምስት ቀናት ቅዳሜ ከሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ከሰዓት በተለያዩ የሥነ ጥበባት ጉዳዮች ላይ በርካታ የውይይት መድረኮችን ሲያካሂድ መቆየቱን ለተሳታፊዎች ገልጸዋል።
በእለቱ ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ባሻገር ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት በአጻጻፍ ስልት፣ በታሪክ አወቃቀር እና በሌሎች የሥነ ጽሑፍ አላባዊያን ላይ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ እንዲሁም በአማርኛ ድርሰት የተራቀቁ ደራሲያን ሥራዎች ላይ ያተኮረ ሙያዊ ትንታኔ በኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ ፕሬስ አርታኢ፣ ደራሲና ተርጓሚና አቶ ቴዎድሮስ አጥላው ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
የውይይቱ ዐቢይ ዓላማ ከአማርኛ ሌላ በሆነ ቋንቋ ሥነ ልሳናዊ ባህሪ ውስጥ አድገው አማርኛን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ተምረው በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ የተራቀቁ ደራሲያን ያበረከቷቸውን አስተዋጽዖች በመጠኑ ማስተዋወቅና በምርምር ወይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ደረጃ ሊሠራ ስለሚገባ ጥናት መቆስቆስ እና መነሻ የሚሆኑ ነጥቦችን ማቀበል እንደሆነ አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል።
የዚኽ ዓይነት ልምድ ከሀገር አቀፍ ባሻገር በዓለም አቀፍም ደረጃም ተደራሽነትን እና ተቀባይነትን ለማሳደግ ወይም በግላዊ ፍላጎት ብዙ ደራሲያን ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሌላ በሆኑ ቋንቋዎች ብዙ መጽሐፍት መድረሳቸውን ጠቅሰው በሀገራችን እንደ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር፣ በዓሉ ግርማ፣ ጸጋዬ ገብረመድኅን፣ አማረ ማሞ እና ሌሎችም ወጣት ደራሲያን የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አማርኛ ያልሆነ ግን ለአማርኛ ድርሰት እድገትና መዘመን ጉልህ አበርክቶ እንደነበራቸው አብራርተዋል፡፡


የውይይት መድረኩ ዓላማ የሥነ ልሳንና የሥነ ጽሑፍ ተመራማሪዎችን ለሰፊና ጠንካራ ጥናት መጋበዝ የሚችል በመሆኑ አጥኚዎች በተለይም ልሳነ ብዙ ደራሲያን በሠሩበት አኳኋን ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ጋር በማነጻጸር አንዱ ልሳን ለሌላው ልሳን መነሻ በመሆን ለኢትዮጵያ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት ያሳደራቸውን አስተዋጽዖዎች አጥኚዎች በንጽጽራዊ ጥናት እንዲገመግሟቸው አቶ ቴዎድሮስ አስታውሰዋል፡፡
ከተሳታፊዎች ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የሕትመት ዋጋ መናር ለበርካታ ደራሲያን ተግዳሮት መሆኑ ለሕትመት ሥራ መቀዛቀዝና የአንባቢ ቁጥር መቀነስ መንሳዔ መሆናቸው ተጠቁሟል። ለተጠቀሱ ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት ኪነ ጥበብብም እንደ ሌሎች የሥራ ዘርፎች ራሱን ችሎ የኢንቨስትመንት እንዲሆን ከሳይንስ አካዳሚ፣ ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የኪነ ጥበብብ እንዲሁም የሕትመት ፖሊሲ ጥናቶችን በማድረግ መፍትሔ ለመፈለግ ቢሮው በሚችለው መንገድ እንደሚሠራ አቶ ሠርጸ ፍሬስብሐት አሳውቀዋል፡፡