ፀሐይ:- የኢትዮጵያ አቪዬሽን አጀማመር

“ፀሐይ፡- የኢትዮጵያ አቪዬሽን አጀማመር”

አዲስ መጽሐፍ

ደራሲ፡- ካፒቴን ዘላለም አንዳርጌ

አሳታሚ – የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አንድ ክንፍ የሆነው የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ፣ በኢትዮጵያ ሳይንሳዊ እውቀትን ለማስፋፋት፣ ምርምሮችን ለማበረታታት እና ሳይንስን የባህሎቻችን አካል ለማድረግ የሚረዱ መጻሕፍትን መርጦ፣ በባለሙያዎች አስመርምሮ እና አስገምግሞ፣ እንዲሁም በጥልቅ የአርትዖት ሒደት አሳልፎ በከፍተኛ ጥራት ያሳትማል፡፡ ይህ በካፒቴን ዘላለም አንዳርጌ የተጻፈው የአቪዬሽን ታሪክ መጽሐፍም በዚህ ሙያውን ጠብቆ በተከናወነ ሒደት አልፎ የታተመ፣ የታሪክ ክፍተትን የሚሞላ ሥራ ነው፡፡

መጽሐፉ ከዚህ በፊት በተበታተኑ ጥናቶች ካልሆነ በቀር፣ በተለይ በአገር ውስጥ ቋንቋ በወጉ ያልተጻፈው፣ ከ1921-28 ያለው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ታሪክ ላይ የሚያተኩር እና ይህንኑም በዝርዝር በጥልቀት ይተነትናል፡፡ በማዕከላዊነት ደግሞ “ፀሐይ” በተባለችው እና በ1928 እዚሁ አገር “ተሠርታ” አገልግሎት ከመስጠቷ በፊት በኢጣሊያ ወረራ ምክንያት ወደ ሮም የተወሰደችው አውሮፕላን በምን መነሻ እና በማን እንደተሠራች፣ አገነባቧ እንዴት እንደነበረ፣ ከኢትዮጵያውያን መካኒኮች በግንባታዋ ላይ እነማን እንደተሳተፉ፣ ተሠርታ ስትጠናቀቅ ስለነበራት ገፅታ፣ በወረራው ጊዜ እንዴት ወደ ኢጣሊያ እንደተወሰደች፣ አሁን የት እና በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች በዝርዝር ይተርካል፡፡

በፀሐይ አማካይነት ኢትዮጵያውያን የሥልጣኔ ማለዳ ላይ እንደነበሩ በማሳየት በትውልዱ ላይ ቁጭት ለማሳደር ይጥራል፤ ፀሐይን ወደ አገሯ ማስመለስ ቅርስን ብቻ ሳይሆን የሥልጣኔ ምልክታችንን ማስመለስ እንደሆነም በአፅንዖት ይገልጻል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም፣ በኢትዮጵያ አቪዬሽን ታሪክ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከቱ የውጭ አገር ባለሙያዎችን በልካቸው ይዘክራል፤ የተጋነነ ታሪክ ተጽፎላቸዋል ያላቸውን የውጭ አገር ባለሙያዎች ታሪክ ደግሞ በማስረጃዎች አስደግፎ ይሞግታል፡፡

በዋነኛነትም በታሪካችን የመጀመሪያዎቹን ኢትዮጵያውያን የበረራ ተማሪዎች እና ትምህርት ቤቶች፣ የመጀመሪያዎቹን አውሮፕላኖቻችንን እና አብራሪዎቻቸውን፣ የመጀመሪያዎቹን ኢትዮጵያውያን የአውሮፕላን መካኒኮች ታሪኮቻቸውን፣ በፎቶግራፎች እና በንድፎች አስደግፎ ይዘክራቸዋል፡፡ ለአውሮፕላኖቹ የሕይወት ታሪኮች፣ ከአብራሪዎቹና ከመካኒኮቹ የሕይወት ታሪኮች ባልተናነሰ ትኩረት ይሰጣል፡፡

“ፀሐይ” በመጻሕፍት፣ ባልታተሙ የግል ማስታወሻዎች፣ በጥንት ጋዜጦችና መጽሔቶች፣ በጥናት ጽሑፎች እና በቃለ መጠይቆች የዳበረ፣ ከኢትዮጵያ ታሪክ ክፍተቶች አንዱን የሚሞላ የተዋጣለት መጽሐፍ ነው፡፡

መጽሐፉን ብሔራዊ ቴአትር ጀርባ፣ በዐይናለም የመጻሕፍት መደብር በተመጣጣኝ ዋጋ ያገኙታል፡፡

================================================================

ተፈሪ ዓለሙ ስለ “ፀሐይ” መጽሐፍ በሸገር የቅዳሜ  ጨዋታ  ያቀረበውን ዝግጀት ሙሉውን ለመስማት  ይህን ይጫኑ