የኢፌዴሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎችን ባለሙያዎች ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራን ለሀገራዊ ልማት ለማዋል በጋራ በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከር በኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ዋና መሥሪያ ቤት ጉብኝት አድረገዋል።
የአካዳሚው ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ከሚኒስቴር መሥሪያቤቱ የመጡትን አባላት ተቀብለው ስለ አካዳሚው አጭር መግለጫ ሰጥተዋል፡፡አካዳሚው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በወሳኝና ሀገራዊ ጠቀሜታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን በማድረግና በማስረጃ ላይ የተደገፈ የፖሊሲ ምክር ሐሳብ ለመንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመስጠት ለሀገራዊ ፖሊሲ ቀረጻና ማሻሻያዎች ያበረከታቸውን አስተዋጽዎች ዘርዝረዋል።

አካዳሚው ሳይንሳዊ ዕውቀትና ባህልን በኅብረተሰቡ ለማስረጽ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች ዋና ዋናዎቹ የሳይንሳዊ ገለጻና የፓናል ውይይት መድረኮችን ማካሄድ፣ ምሁራዊ የክርክር መድረኮችን ማመቻቸት እንዲሁም በአካዳሚው ፕሬስ በኩል ሳይንስና ሳይንስ ነክ እውቀቶችን አሳትሞ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕዝብ ማድረስ መሆናቸውን ፕሮፌሰር ተከተል አብራርተዋል።
ከኢትዮጵያ የልማት ግቦች ጋር በማጣጣም እንደ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) ፣ ባዮቴክኖሎጂ፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በመሳሰሉ ሀገራዊ ጠቀሜታ ባላቸው ጉዳዮች ላይም ወደፊት በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ሁለቱም ተቋማት የኢትዮጵያን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በሚያደርጉት ጥረት በምርምር፣ በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማፍለቅና ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ የተጠናከረ ትብብር ማድረግ እንደሚኖርባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሚኒስቴሩ የሀገራዊ ምርምር ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሀብታሙ አበራ በሰጡት አስተያየት ለሁለቱም ተቋማት የጋራ ግባቸው ከሆኑት ተግባራት መካከል ሳይንስን ሕዝባዊ ማድረግ፣ ሳይንሳዊ አካሄድን የተከተለ እና በማስረጃ የተደገፈ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ምክረ ሐሳብ በማመንጨት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት ሥራዎችን በቅንጅት በመሥራት በዘርፉ የታለሙ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት በልዩ ትኩረት መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ዶ/ር ሀብታሙ አያይዘውም ከአካዳሚው ጋር መሥራታችን የኢትዮጵያን እድገት እና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት የሚያጎናጽፍ ምርምርን ከሀገራዊ ፖሊሲዎች እና የቴክኖሎጂ ግስጋሴዎች ጋር በማዋሃድ እንድንሠራ ያስችለናል ብለዋል።
አካዳሚ በአባልነት ያቀፋቸው ሊቃውንት በአካዳሚክስና ዓለም አቀፋዊ ተቋማትን በመምራት ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ በመሆናቸው ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም መንግሥትና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ለተቋማቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ሌሎች ሰነዶች ዝግጅት እንዲኹም የማማከር አገልግሎት በሚፈልጉበት ጊዜ አካዳሚው ይህንኑ አገልግሎት በክፍያ በመሥራት ተቋማዊ አቅሙን በገቢ ማሳደግ እንደሚገባውም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የመጡ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ጠቁመዋል።
ስለ አካዳሚው አጋርነት አስተያየት የሰጡት የአካዳሚው የፕሮጀክት ሥራዎች አስተባባሪ አቶ አበበ መኩሪያው የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በአንድ ወቅት የአካዳሚው አባላት በሀገሪቱ ካሉ ምሁራን መካከል በተሰማሩበት መስክ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ፣ ለሀገራችን የሳይንስ እድገት ወሳኝ ድርሻ የነበራቸው እና በምርምር አገልግሎት የተሻለ ውጤት በማስመዝገባቸው የተመረጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ስብስብ መሆኑን ጠቅሰው የመንግሥት አካላት ይህንን እምቅ አቅም ለመጠቀም በአጋርነት እንዲሠሩ ገልጸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህ መሠረትም በርከት ካሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አካዳሚው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጥናት እንዲያደርግላቸው እና ረቂቅ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን፣ የዩኒቨርስቲ ማስተማሪያ የላቦራቶሪዎችን ደረጃዎችና መመሪያዎች እንዲያዘጋጅላቸው ጥያቄዎች ቀርበው በተሳካ ሁኔታ የተሠራላቸው መሆኑን አውስተዋል።
በመጨረሻም ሁለቱ ተቋማት የጋራ ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ ፕሮጄክቶችን በጋራ በመቅረጽ ለመተግበር የሚያስችል የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ቢቋቋም ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል የጋራ ግንዛቤ በመውሰድ ውይይቱ ተቋጭቷል። በመቀጠልም የሚኒስቴር መሥሪያቤቱ አባላት የአካዳሚውን የሳይንስና የስቴም ማዕከል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችና ኤግዝቢቶች ጎብኝተዋል፡፡