የኢትዮጵያን ግብርናን ለማዘመን የኃይል አጠቃቀምን ደረጃ በደረጃ መለወጥ ያስፈልጋል ተባለ

የኢትዮጵያ ግብርና ሜካናይዜሽን – እያዩ መራመድ በተሰኘ ርዕስ ኅዳር 27/2011 ዓ.ም በዶ/ር መለሠ ተመስገን ገለፃ ቀርቦ፣ ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው የመንግስት ባለሙያዎች፣ የምርምር ተቋማት አጥኚዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ ከህብረተሰቡ የተገኙ እና የሚዲያ አካላት በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በገለፃው የኢትዮጵያ ሥነ ምኅዳራዊና ሶሺዮ-ኢኮኖሚያዊ ገፅታ፣ የግብርና ሜካናይዜሽን ሂደትና ደረጃ፣ የሜካናይዜሽን ሥራ እዳይፋጠን የገደቡት ማነቆዎችና የሌሎች አገራት ልምድ እንዲሁም የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ሥራ ከማዘመን እና የአርሶ አደሩን የምርት ሂደት ከማሻሻል አንፃር መደረግ ስለሚኖርባቸው ጉዳዮች ከላይ ከተገለጹት ባለድርሻ አካላት ጋር ተመክሮበታል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ሜካናይዜሽን – እያዩ መራመድ በተሰኘ ርዕስ ኅዳር 27/2011 ዓ.ም በዶ/ር መለሠ ተመስገን ገለፃ ቀርቦ፣ ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው የመንግስት ባለሙያዎች፣ የምርምር ተቋማት አጥኚዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ ከህብረተሰቡ የተገኙ እና የሚዲያ አካላት በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል፡

በገለፃው የኢትዮጵያ ሥነ ምኅዳራዊና ሶሺዮ-ኢኮኖሚያዊ ገፅታ፣ የግብርና ሜካናይዜሽን ሂደትና ደረጃ፣ የሜካናይዜሽን ሥራ እዳይፋጠን የገደቡት ማነቆዎችና የሌሎች አገራት ልምድ እንዲሁም የኢትዮጵያን  የግብርና ዘርፍ ሥራ ከማዘመን እና የአርሶ አደሩን የምርት ሂደት ከማሻሻል አንፃር መደረግ ስለሚኖርባቸው ጉዳዮች ከላይ ከተገለጹት ባለድርሻ አካላት ጋር ተመክሮበታል፡፡

እንደገለፃው አቅራቢ የግብርና ሜካናይዜሽን ማለት የእርሻ ሥራን ለማቀላጠፍ የሚከናወን የተለያዩ የግብርና መሣሪያዎችን እና ኃይል የመጠቀም ሂደት ነው፡፡ የግብርና ሜካናይዜሽን በሰው፣ በእንስሳትና በሞተር ኃይል በሚንቀሳቀሱ መሣሪያዎች የሚደረግን የምርት ሂደት እንደሚያጠቃልልም አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ 14 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑ አባወራ አርሶ አደሮች በዋናነት ተዋናይ የሆኑበት ሲሆን፣ 80 በመቶ ለሚሆነው ህዝብ የሥራ ዕድል ድርሻ ይይዛል፡፡ ባለው መረጃ መሠረት በዋናነት ከ13-14 ሚሊዮን የሚሆኑ በሬዎችን ኃይል በመጠቀም፣ 14,400 ትራክተሮችን እንዲሁም 1,150 ኮምባይነር የምርት መሰብሰቢያ ማሽኖችን ለግብርና ሥራ በማዋል 40 በመቶ ጥቅል አመታዊ ምርት እና 80 በመቶ ለወጪ ምርት ድርሻ አለው፡፡

#የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን የተሻሻሉ የማሳ ላይ የኃይል አማራጮችን ለመጠቀምና የምርት መጠንን ለመጨመር ብሎም የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመለወጥ ማነቆዎች መግጠማቸው አልቀረም; ያሉት ዶ/ር መለሠ፣ አነስተኛ የመሬት ይዞታና የተበጣጠሰ ማሳ፣ የሜካናዜሽን መገልገያ መሳሪያዎችን ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የምንዛሪው መጠን ያለማቋረጥ መጨመር፣ በብርዕ ሰብል ላይ ያተኮረ ግብርናና የአርሶ አደሩ የገቢ አቅም ውሱንነት፣ የምርት ማጓጓዣ መንገድ ዝርጋታ ማነስ፣ የጥገና ክህሎትና መሰረተ ልማት እንዲሁም የመለዋወጫ እጥረት፣ የአፈሩ መበላትና መሳሳት፣ የኢንዱስትሪውና የአገልግሎቱ ዘርፍ በበቂ ሁኔታ ያለማደጉ እና በዘርፉ ለመሠማራት የባንክ ወለድ ከፍተኛ መሆን ዋነኞች እንደሆኑ አቅራቢው ይጠቅሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ በጠቅላላ ለእርሻ አመቺ የሆነው መሬት 74.5 ሚሊዮን ሄክታር ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ እየታረሰ ያለ 13.5 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ ነው፡፡ ይህ መሬት ባብዛኛው በሥራ ላይ ያልዋለው አቀማመጡ በአብዛኛው ለሰውና ለከብት አመቺ ባለመሆኑና በውሃ እጥረት ምክንያትም እንደሆነ በገለፃው ተነስቷል፡፡ በመሆኑም ዋናው ትኩረት ያልታረሱ መሬቶችን ለማልማት ለእርሻ አስፈላጊ የሆኑ ዘመናዊና ከፍተኛ ኃይል ያላቸውን መሳሪያዎች በመጠቀም አስተራረሱም እንደ አፈሩና ሥነ ምህዳሩ አይነት ለዘላቂ እርሻ አመቺ በሚሆንበት መንገድ ማስፋፋት ሲሆን፤ የውሀ እጥረት ባለባቸው ሥፍራዎች ደግሞ መስኖን ማስፋፋት መሆን ይኖርበታል፡፡ ዶ/ር መለሠ በገለፃቸው እንደምሳሌ በመጥቀስ ስትራቴጂው በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ እሰከ 20 ሚሊዮን ተጨማሪ መሬት በከፍተኛ ሜካናይዜሽንና መስኖ አጠቃቀም ለእርሻ በማልማት ከአገር ውስጥ ፍጆታና ገበያ ተርፎ ምርትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ማቀድ የተሻለ ነው ብለዋል፡፡ የእነዚህ ሰፋፊ እርሻዎች መልማት በርካታ አግሮኢንዱስትሪ ለማስፋፋት አንደሚያስችልና በዚህም ከፍተኛ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር፤ በሂደትም በተለምዶው የእርሻ ሥራ ላይ የተሰማራውን ህዝብ ቁጥር በመቀነስ ግብርናን ለማዘመን የሚያስፈልገውን ቅድመ ሁኔታ እያሟሉ መጓዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

አቅራቢው ትራክተርን ለእርሻ መጠቀም ብቻ በራሱ ምርታማነትን እንደማይጨምር በምርምር የተረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ በትራክተር ማረስ የሚያስፈልገው አርሶ አደሩ ማሳውን በበሬ አርሶ በወቅቱ ማጠናቀቅ የማይችል ከሆነ ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ማሳቸውን በወቅቱ ማዘጋጀት ለማይችሉ አርሶ አደሮች ትልቅ አቅም ያላቸውን ትራክተሮች በኪራይ መልክ እንዲቀርብላቸው ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ የአንዳንድ ሀገሮችን ልምድ በመጥቀስ አርሶ አደሮች በትራክተር ማረስን እየተው በበሬ ማረስ በመጀመራቸው ሂደቱን ቆም ብሎ በማሰብና አነስተኛ ማሳዎችን በበሬ በሚጎተቱ የተሻሻሉ ማረሻዎች በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ቅድሚያ ሊሰጠው ያስፈልጋል በማለት ለተሳታፊዎች አብራርተዋል፡፡ በሂደት ግን  ይላሉ ዶ/ር መለሠ «የኢንዱስትሪውና የአገልግሎት ዘርፉ ማደግ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ፈጥሮ በገጠሩ የሚኖረው ህዝብ ቁጥር ሲቀንስና ማሳዎቹ በስፋት ማልማት በሚችሉ ጥቂት ሰዎች እጅ ሲገቡ እንደሌሎች ሀገሮች ከፍተኛ ደረጃ ያለው ሜካናይዜሽን መጠቀም ይቻላል» በማለት የሜካናዜሽንን ዕድገት ደረጃ አሳይተዋል፡፡

ዘመናዊ የድህረ ምርት መሳሪያዎች ማለትም ኮንባይነሮች፣ ቋሚ የእህል መውቂያዎች፣ የበቆሎ መፈልፈያዎች ምርትን በወቅቱ ለመሰብሰብ ከማስቻላቸውም በተጨማሪ ብክነትን በመቀነስ ምርታማነትን የሚጨምሩ በመሆኑ በስፋት የሚቀርቡበት መንገድ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችና በሀገር ውስጥ ለሚፈበረኩ መሳሪያዎች ግንባታ የሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎች ወደሀገር ውስጥ ያለቀረጥ እንዲገቡ መፍቀድ በፖሊሲ ደረጃ እንደ መፍትሄ ሊወሰድ ይገባዋል በማለትም አቅራቢው አመላክተዋል፡

የሆነ ሆኖ #የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ለዘመናት የተከተሉት በእንስሳት ጉልበት የሚደረግ አስተራረስ ከድህነት ማስወጣት ስላልቻለና ሰፊ ሊለማ የሚችል የመሬት ሐብት በመኖሩ የግብርናው ዘርፍ የሥርዓት ለውጥ ይፈልጋል;  እና #ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር መናር አሳሳቢ በመሆኑ፣ ይህንን ግዙፍ ቁጥር ለመመገብ ዘመናዊ የማረሻ፣ የመዝሪያ እና የምርት መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂ ማለማመድና መጠቀም ያስፈልጋል; የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ተነስተዋል፡፡

1

አቅራቢው ዶ/ር መለሠም የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማዘመን በመስኩ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ከቀበሌ ልማት ሰራተኞች ጀምሮ እሰከ ግብርና ቢሮዎች ድረስ መመደብ ያስፈልጋል፤ ለዘርፉም አሁንም የተለየ ትኩረት መስጠትና በምርምር የታገዘ አዲስ ዕይታ ማምጣት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

24

የ36ኛ ዙር የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረክ ዶ/ር ሰሎሞን ኃይለማርያም የገለፃው አወያይ የነበሩ ሲሆን፣ በቀጣይነትም በዚህ አገራዊ ጉዳይ ላይ ከሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አካዳሚው ተጨማሪ መድረኮችን እንደሚያመቻች ገልፀው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *