በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ በአስተዳደር፣ ዲፕሎማሲ እና ሥነ ጽሑፍ መስክ ላይ ደማቅ አሻራ ጥለው ያለፉትን የታላቁን የሀገር ባለውለታ የክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴን አበርክቶ የሚዘክር የመታሰቢያ ሐውልት ሐምሌ 9 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ቅጥር ግቢ ውስጥ በይፋ ተመርቋል። በዚሁ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የቤተሰብ አባላት፣ የአካዳሚው መሥራቾች፣ የቀድሞና የአሁኑ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።

አካዳሚው በአሁኑ ወቅት የእኒኽን ታላቅ ሰው ታሪካዊ መኖሪያ ቤት በቅርስነት እየተንከባከበ በዋና መሥሪያ ቤትነት እየተጠቀመበት ይገኛል። በተጨማሪም ለሀገራቸው ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ ተገቢውን እውቅና ለመስጠት የሥነ ጥበብ ማዕከሉን በስማቸው በመሰየም ታሪካቸውን በመሰነድ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍም ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ከቤተሰቦቻቸውና አካዳሚው ከሌሎች አካላት ያሰባሰባቸውን ጠቃሚ ሰነዶችን፣ ታሪካዊ ፎቶግራፎችን፣ የድርሰቶቻቸውን የመጀመሪያ ረቂቆች፣ የታተሙ መጻሕፍትና ሌሎች ቅርሶችን የያዘ ቋሚ ሙዚየም በማደራጀት ለጎብኚዎች ክፍት አድርጎ ይገኛል።
በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር በላይ ካሳ እንደገለጹት፣ ክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በሀገራችን ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ እና የቴአትር ጅማሮ ውስጥ ጉልህ ሚና ያላቸውየጥበብ ሰው ናቸው። ከዚህም ባሻገር በዘመናዊ የባንክ ምሥረታ ላይ የበኩላቸውን የጎላ አሻራ ያሳረፉ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርን በመሪነት ያገለገሉ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓት ላይ የራሳቸውን አወንታዊ ሚና የተጫወቱ ሁለገብ ሊቅ መሆናቸውን አብራርተዋል። ፕሮፌሰር በላይ አክለውም፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ አዲስ አበባ ከተማን በዳይሬክተርነት ወይም በአሁኑ አጠራር በከንቲባነት ማዕረግ ማገልገላቸውን አስታውሰዋል። በዲፕሎማሲው ረገድም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ብቸኛዋ ነጻ ሀገር መሆኗ ታምኖበት የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል እንድትሆን አሻራቸውን ያሳረፉ፣ ከአምባሳደርነት እስከ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሀገራቸውን በታማኝነትና በብቃት ያገለገሉ ምርጥ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአካዳሚው ቅጽር ውስጥ ለመታሰቢያ የቆመላቸው ሐውልት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ ሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህር እናየዕይታ ጥበብ ባለሙያ በሆኑት በሠዓሊ ኢዮብ ኪታባ ንድፍ አውጪነት (Artistic Direction & Concept Design) እና መሪነትና በቡድናቸው የተቀረጸሲሆን አካዳሚው ይሕ ሐሳብ እውን እንዲሆንና ለምረቃ እንዲበቃ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የልጅ ልጅ ልጅ ለወይዘሮ ገነት ኅሩይ የላቀ ምስጋና ቀርቦላቸዋል። ወይዘሮ ገነት ይህንን ታሪካዊ ሥራ ከዳር ለማድረስ ላደረጉት ከፍተኛ ጥረትና ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖ ከአካዳሚው የእውቅና ሰርተፊኬትም በእለቱ ተበርክቶላቸዋል።
በመጨረሻም፣ የዚህን አስደናቂ የመታሰቢያ ሐውልት የቅርጽ ሥራ ለነደፉትና ቀርጸው ላቆሙት ለሠዓሊ ኢዮብ እና ለቡድናቸው እንዲሁም በአማካሪነት ላገዙት የአካዳሚ የሥነ ጥበባት የሥራ ቡድን ሰብሳቢ ለፕሮፌሰር በቀለ መኮንን እንዲሁም ሥራው ስኬት አስተዋጽዖ ላደረጉት የጥበብ ባለሙያዎች በሙሉ አካዳሚው የላቀ ምስጋናውን አቅርቧል።





