የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሳይንስና ቴክኖሎጂ የጽንሰ ሐሳብ አቻ ስያሜዎችን ከብያኔዎቻቸው ጋር የያዘ “አዲስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ” መዝገበ ቃላት አስመረቀ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ይህንን የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንግሊዝኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት ያዘጋጀው የሳይንስ ዕውቀትን በማስፋፋትና ሳይንሳዊ ባህልን በማዳበር ተልእኮውን በመፈጸም ሂደት ዓይነተኛ ግብዓት ለማበርከት ዐልሞ ነው፡፡ ፕሮጀክቱን ሲነድፍም መዝገበ ቃላቱ ወደ ፊት በሌሎች ሀገርኛ ቋንቋዎችም ተተርጉሞ ሰፋ ላለ ኅብረተ ሰብ አገልግሎት እንደሚሰጥ ታሳቢ በማድረግ ነው።

ይህንን ተግባር ማከናወን ያስፈለገበት ዋናው ምክንያትም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እያደገ በመምጣቱ እና በሀገራችን የትምህርት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የምርምር ዘርፎች ጉልህ የሆኑ ለውጦች እየታዩ በመሆናቸው በቋንቋ ምክንያት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሐሳቦችን የመግለጽ ዐቅም ማዳበር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ ከ30 በላይ የሙያ ዘርፎች ከ90 በላይ ከከፍተኛ ትምህርት፣ ከምርምር ተቋማት እና ከሳይንስ አካዳሚ የተመረጡ ዕውቅ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ከ11,500 በላይ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስያሜዎች የተበየኑበትን መዝገበ ቃላት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዳራሽ በርካታ ተሳታፊዎች በተገኙበት ኅዳር 1 ቀን 2018 ዓ .ም አስመርቋል፡፡ የመዝገበ ቃላቱን የሞባይል መተግበርያ የማልማት ሥራ መጀመሩም ተዋውቋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ቁልፍ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሳ  በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይንስ ለመላው የሰው ልጆች ዕድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽዖ እና ዓለምን ለጋራ ዓላማ የማስተባበር ኃይሉ በመላው ዓለም በሚዘከርበት የዓለም የሳይንስ ቀን፤ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዕውቀት ፈጠራ እና ሥርጭት ረገድ በሀገራችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረውን መዝገበ ቃላት አካዳሚው ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በማስመረቁ ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ ተልእኳችን በመላው ኢትዮጵያ የሳይንስን ባህል፣ ዕውቀት እና ኢኖቬሽንን ማስፋፋት ሲሆን፤ ይኽ “አዲስ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የእንግሊዝኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት” ይህንን ተልእኮ በመወጣት ረገድ ይኽ ሥራ ከአካዳሚው ጥረቶቻች አንዱ መሆኑን አሳውቀዋል። ይኽም በየጊዜው እያደገና እየተሻሻለ የሚኼድ ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ነው ብለዋል።

መዝገበ ቃላቱ በአካዳሚው እና በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አጋርነት ዛሬ እንዲህ በመጽሐፍ ተደጉሶ፣ በመተግበሪያም ዘምኖ የተዘጋጀው በርካታ ምሁራን እና ባለሙያዎች ዕውቀት፣ ክህሎት እና ትጋታቸውን አስተባብረው ለጋራ ዓላማ በማዋላቸው እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ጠቁመው፣ በዚህ ፕሮጀክት ላይ ቃላትን መርጠው ላደራጁት እና በጥንቃቄም ለተረጎሙት ከ90 በላይ የየሙያው እና የቋንቋ ባለሙያዎች፤ እንዲሁም ጥራቱን ለማስጠበቅ ለተጉት ከ50 በላይ ለሚኾኑት ገምጋሚዎች፣ አርታኢዎች እና የፕሮጀክት አስተባባሪዎች በሙሉ ጥልቅ እና ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።

የዚኽ መዝገበ ቃላት ፕሮጀክት እንደማንኛውም የፕሮጀክት ውጤት የሚቆጠር ሳይኾን ዕውቀትን ለማስፋፋት፣ ፈጠራን ለማነቃቃት እና ማኅበረሰባዊ ዕድገትን ለማፋጠን  አካዳሚው ያለውን  ቁርጠኝነት ማሳያ ሕያው ምስክር መሆኑን አንስተው በምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙትንና እና በመጽሐፉ ዝግጅት ሥራ የተሳተፉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብሎም የሀገራችን አንጋፋ ምሁራን አመስግነው ቅንጅታዊ አሠራሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፕሮፌሰር በላይ  መልእክት አስተላልፈዋል።

በመጽሐፉ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ አዲሱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንግሊዘኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላት መጽሐፍ ሕትመት ተከናውኖ ለምረቃ መብቃቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍን በመረዳት ወደ ተግባር ለመለወጥ ለሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

መዝገበ ቃላቱ በቀጣይ በብዙ የሀገራችን ቋንቋዎች እየተተረጎመ ተደራሽ እንዲሆን ለማስቻል ከኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ እና ሌሎች ተመሳሳይ ዓላማና ተልእኮ ካላቸው ተቋማት ጋር በትብብር መሠራት እንዳለበት አሳውቀዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉቀን ቀሬ በበኩላቸው መዝገበ ቃላቱ በዓለማችን ላይ እየረቀቀ የመጣውን የሳይንሳና ቴክኖሎጂ እድገት ከራስ አውድ ጋር በማስማማት በሀገር አቀፍ ደረጃ በቀላሉ ለማዳረስ ጠቃሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

አያይዘውም፣ ሀገራዊ ቋንቋዎችን ለእነዚህ አገልግሎቶች ለማብቃት ሳይንሳዊ ዕውቀትንና ፅንሰ ሐሳቦችን የሚያስፋፉ ጽሑፎችን በሀገርኛ ቋንቋዎች በመድረስም ኾነ በመተርጎም ለኅብረተ ሰቡ በስፋት ማቅረብ አስፈላጊ እንደሆነም አክለዋል፡፡

ስለመዝገበ ቃላቱ የዝግጅት ኺደት ማብራሪያ የሰጡት የመጽሐፉ ፕሮጀክት መሪና የአካዳሚ ፕሬሱ የኤዲቶርያል ቦርድ አባል ዶ/ር ታየ አሰፋ በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት ከሚስፋፋባቸውና ሳይንሳዊ ባህልም ከሚዳብርባቸው መንገዶች አንዱ በኅብረተ ሰቡ ውስጥ በስፋት የሚነገሩ ሀገራዊ ቋንቋዎች ሳይንሳዊ ፅንሰ ሐሳቦችን ወርሰው መግለጽ በሚችሉበት ደረጃ ሲበለጽጉና፤ በተለይም በትምህርትና ምርምር መስተጋብር፣ በመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ፍሰት፣ በፖሊሲ ቀረጻና አፈጻጸም፣ በልማት ዕቀዳና አተገባበር፣ በንግድና ኢንዱስትሪ፣ እንዲሁም በግብርናና በጤና ዘርፎች በሚደረጉ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ብቁ የተግባቦት መሣሪያ መኾን ሲችሉ ነውብለዋል፡፡

 በውጭ ቋንቋዎች ለሚገለጹ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስያሜዎችም በሀገርኛ ቋንቋዎች አቻ ስያሜዎችን በመቅረጽና የፅንሰ ሐሳቦችን ምንነት በመተርጎም የሚያቀርቡ መዛግብተ ቃላት ማዘጋጀትና ለትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ ለሌሎች ባለድርሻ አካላት፣ ለቤተ መጻሕፍትና ለተለያዩ ተጠቃሚ የኅብረተ ሰብ ክፍሎች ማስተዋወቅና ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖ እንደታተመ ዶ/ር ታየ አብራርተዋል።

በሁለቱ ተቋማት ትብብር ታትሞ ለንባብ  የበቃውን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላትና የሞባይል መተግበሪያውን እጅ ለእጅ ተያይዞ ዕውቀትን እና ኢኖቬሽንን ለማሳደግ ከማገዙም በላይ፤ በሳይንሳዊ ዕውቀት እና በኢኖቬሽን ላይ ተመሥርቶ የራሱን የወደፊት አቅጣጫ ለመንደፍ እና ለመቅረጽ የሚችል የተማረ ማኅበረሰብ ለመገንባት በተቋማቱ ዘንድ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል ተብሏል።