የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና የአእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን በትብብር ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ

ስምምነቱን የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ወልዱ ይምሰል እና የአካዳሚው ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ በአካዳሚው ቅጥር ግቢ ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ በአሁን ወቅት በሀገራችን የሚስተዋለውን ዝቅተኛ የኣእምሯዊ ንብረት ግንዛቤ ለማሻሻል፣ የጥናትና ምርምር ውጤቶች የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ለማጠናከር፣ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አብረው ለመሥራት ታስቦ እንደተፈጸመ ተገልጿል።

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ድጋፍ ማዕከል /TISC/ የማቋቋም፣ የፓተንትና ቴክኖሎጂ መረጃዎች ተደራሽነት፣ ግንዛቤ እና ተያያዥ ጉዳዮች በመግባቢያው በዋናነት የተካተቱ መሆናቸው በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

አካዳሚው አካዳሚያዊ እና ሳይንሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በፕሬሱ በኩል ሳይንስና ሳይንስ ነክ እውቀቶችን አሳትሞ በቀላል ዋጋ ለሕዝብ የሚያደርሳቸውን መጻሕፍትና የጥናት ውጤቶችን የፓተንት መብት ለማስጠበቅ ከባለሥልጣን መሥሪያቤቱ ጋር በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ የአካዳሚው ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ገልጸዋል።

የባለስጣኑ ዋና ዳይሬክተር አካዳሚው በወሳኝ ሀገራዊ ጠቀሜታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ያበረከታቸውን አስተዋጽኦዎችን አድንቀው ይህንን ለመደገፍና የምርምርና ጥናት ውጤቶች ወደ ምርትና ገበያ እንዲሸጋግሩ ለማስቻል የአእምሯዊ ንብረት ምዝገባና ጥበቃ ወሳኝ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

አያይዘውም አካዳሚያዊ ተቋማት የፈጠራ ሥራዎች መፍለቂያ ቦታዎች በመሆናቸው የአእምሯዊ ንብረት ለማመንጨት ትልቅ አቅም መሆናቸው ቢታመንም እስካሁን ባለው መረጃ በኢትዮጵያዊያን የሚቀርቡ የአዳዲስ የፓትንት ማመልካቻዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።