መርሐግብሩን በእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክታቸው ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሳ ፌስቲቫሉን አካዳሚው ከአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ ሳሙኤል ይርጋ ሪከርድስ (SAY Records), ዘመን ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮምና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር “ሥነ ጥበብን እናክብር፣ እንሥራ ጠቢብ እንሁን’’ በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ለሁለተኛ ጊዜ በዓለም ደረጃ ለሰባተኛ ጊዜ በአካዳሚውና ተባባሪ አካላት ለሁለተኛ ጊዜ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ፌስቲቫሉ ለሥነ ጥበባት ማሳያ መድረክ ብቻ ሳይሆን የባህል ልውውጥ እና የማህበረሰብ ተሳትፎን የሚያበረታታ፣ በተለያዩ ክፍለ ዓለማትና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተሰማሩ አካላትን የሚያስተሳስር ዘርፍ መሆኑን ጥቁመው ለዚኽ ዝግጅት ስኬት የተባበሩ አካላትን በአካዳሚው ስም አመስግነዋል።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በመክፈቻ ንግግራቸው ዓለም የሥነ ጥበብ ቀንና የኢትዮጵያ ጃዝ ፌስቲቫል የፈጠራ ባህል ብቻ ሳይሆን ጥበብ ሰውን ለበጎ ተግባር ለማነቃቃት፣ ለማነሳሳትና ለመለወጥ ያለውን ሀይል እውቅና ለመስጠት ጭምር ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል። አያይዘው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሚያዝያ 15 ቀን የተመረጠው የጥበብ ስኬት እና ፈጠራ ምልክት የሆነውን የሊዮናርዶ ዳ ቪንቺን ልደት ለማክበር ነው ብለዋል።

በፌስቲቫሉ ላይ በርካታ የመንግሥትና መንግግሥታዊ ያልኾኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮችና የኢትዮጵያ ጃዝ ሙዚቃ አባት የሆኑት አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄና በርካታ የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል። በፌስቲቫሉ የሥዕል ኤግዚቢሽን፣ የሕፃናት የሥዕል ልምምድና የኢትዮ ጃዝ ኮንሰርቶች የቀረቡ ሲሆን ታዋቂ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ሙዚቀኞች ማራኪ ትርኢቶችን አሳይተዋል።


ዛሬ እሁድ ሚያዝያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ ማራኪ ትርኢቶች ስለሚቀርቡ የመግቢያ ክፍያውም በተባባሪ አካላት ስለተሸፈነ እሁድን በውብና ማራኪ ግቢያችን እንዲያሳልፉ በአክብሮት እየጋበዝን በዚኽ አጋጣሚ የሀገራችንን የሥነ-ጥበባት ሥራዎችን ለማስተዋወቅ ከተለያዩ የስዕል ክምችቶች መካከል የተመረጡ ስእሎችን ለተከታታይ 15 ቀናት እስከ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለእይታ ክፍት አድርገን እንደምናቆይ እናሳውቃለን።

