መንግሥትና ሀብት በተሰኘ መጽሐፍ መነሻነት የፓናል ውይይት ተካሄደ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከዋልያ መጻሕፍት ጋር በመተባበር በዶ/ር ብርሃኑ በሻህ ተጽፎ የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ ባሳተመው “መንግሥትና ሀብት” በተሰኘ መጽሐፍ መነሻነት የፓናል ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የሀገር ሀብት ነጻነት፣ የመዋቅር ለውጥ፣ ግሽበት፣ የሰው ሀብት ልማት፣ ባህል እና የአካባቢ ጥበቃን ስለመሳሰሉ አርእስተ ጉዳዮች ላይ ባለሙያዎች ገለጻዎቻቸውን አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል።

በአፍሪካ ጥናቶች ረ/ፕሮፌሰር ዶ/ር ሙሐመድ ሀሰን፣ የኢንዱስትሪያል ምሕንድስና ተ/ፕሮፌሰር ዶ/ር እሸቴ ብርሃን፣ የትምህርትና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ ዶ/ር ጌታሁን ጋረደው ገለጻዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆኑ የማህበራዊ ልማት ረ/ ፕሮፌሰር ዶ/ር ፋሲል ንጉሤ ፓናል ውይይቱን መርተዋል።

በውይይቱ ላይ በርካታ የምጣኔ ሀብትና የተመሳሳይ ዘርፎች ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። በዕለቱ መጽሐፉ የያዛቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች መሠረት ያደረጉ ዳሰሳዎች ከተለያዩ የሙያ መስኮች በተመረጡ ባለሙያዎች የቀረቡ ሲኾን፤ መጽሐፉ በርካታ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ከነመፍትሔዎቻቸው የዳሰሰ ሳይንስን በአማርኛ ያቀረበ መጽሐፍ እንደሆነ በምሑራኑ ተገልጿል።

መጽሐፉ ባሕልን፣ የአካባቢ ጥበቃን፣ የሰው ሀብት አስተዳደርን፣ ለሁለንተናዊ የሀገር ሀብት ክምችት መንስኤው ብልሀት እንደሆነ የጠቆመና ቀጣዩ ትውልድ ከሀብት ብክነትና ከሀብት እጥረት ራሱን መከላከል የሚችልበትን ብልሀት ያመላከተ መሆኑም ተብራርቷል።

ይኽ መጽሐፍ በይዘቱ አካዳሚያዊ ስለሆነ ቀጥተኛ ተደራሽነቱ ለምሁራን፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለልሂቃን ሲሆን ሁሉም በሙያ ዘርፋቸው ተንትነው ቢተገብሩት ለሀገር እድገትና ለሕዝብ ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑም ተጠቁሟል።

ደራሲው የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፎች ከፋፍሎ የሚያቀርብ ሲኾን፤ እያንዳንዱ የምጣኔ ሀብት ዘርፍ የሀብት አሠራር ነጻነት ኖሮት ለሀገሪቱ እድገት አስተዋጽኦ ማድረግ የሚቻልበትን አካሄድ መርምሮ የሰጠውን አስተያየት ተመራማሪዎች አድንቀዋል።

በመጨረሻም በእስካሁኑ ሀገራዊ አጠቃላይ ልማትን ለማምጣት በተተገበሩ ፖሊሲዎች የተስተዋሉ ጉድለቶችን እንደ ዕድል፣ ጠንካራ ጎኖችን እንደ አቅም በመጠቀም፤ በሀገሪቱ የእድገት ጕዞ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚቻልባቸውን አቅጣጫዎች የጠቆመ መጽሐፍ ስለሆነ ሁሉም ቢያነበውና ቢተገብረው ጠቃሚ ነው ሲሉ በርካቶች መክረዋል።