በደርግ ዘመነ መንግሥት እስከ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ድረስ በተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች ላይ ያገለገሉት የሌ/ኮ ብርሃኑ ባይህ የግለታሪክ መጽሐፍ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያልተነገሩ እና ከተነገሩትም መሐል በአዲስ አተያይ እና በስፋት የቀረቡ የታሪክ መረጃዎችን የያዘ ትልቅ መጽሐፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ ከእስከዛሬ መጻሕፍቱ በተለየ፣ በርካታ ታላላቅ ምሑራንን በአሰናጅነት አስተባብሮ ለሕትመት ያበቃው ይህ መጽሐፍ ሰፊ የታሪክ ክፍተትን እንደሚሞላ፣ አሻሚዎቹንም እንደሚያጠራ ያምናል፡፡
የአሳታሚው ልዩ መግቢያ
“ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ” በሚል ርእስ ለተዘጋጀው ረቂቅ የግድ ደራሲው ከአቀረበው መግቢያ በተጨማሪ፣ በሚከተሉት ምክንያቶች የአሳታሚው መግቢያ ያስፈልገው ነበር።
ሌ/ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እንግዳ፣ የደርግ አባል በነበረበት ዘመን፣ የተለያዩ የመንግሥት ሐላፊነት ሥልጣን ነበረው። የደርግ መንግሥት በፈረሰበት ወቅት ጣልያን ኤምባሲ ውስጥ ከተጠለሉት ጥቂት የደርግ ባለ ሥልጣናት አንዱ ነው።
ስለሆነም ደርግ ከሥልጣን ከወረደበት ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ጀምሮ ይኽ መጽሐፍ ለኅትመት እስከበቃበት ጊዜ ድረስ በጥገኝነት ጣልያን ኤምባሲ ውስጥ ይገኛል። ምንም እንኳን እሱ ጣልያን ኤምባሲ ውስጥ ለዘመናት ቢቀመጥም፣ ‹‹እነሱን ለመጠየቅ አይቻልም›› የሚለው መረጃ መሻሩን ባለማወቅ፣ እሱንና ሌላኛውን የአገር ቤት ስደተኛ ለመጠየቅ እንደሚቻል ብዙ ሰዎች የተረዱት ከዓመታት በኋላ ነበር። በዚህ ጊዜ ከጠያቂዎች አንዱ (ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ) ብርሃኑ ባይህ ስለ ሕይወት ጉዞው የመጽሐፍ ረቂቅ ማዘጋጀቱን ለማወቅ በቃ። ግለሰቡም የመጽሐፉን ረቂቅ “ኤሌክትሮኒክ” ቅጅ ለማንበብ ከብርሃኑ ባይህ ፈቃድ ጠይቆ፣ ረቂቁን ከኤምባሲው ለማውጣት ቻለ።
ፕሮፌሰር ሽብሩ፤ የዚህ መጽሐፍ ባለታሪክ ብርሃኑ ባይህ ተግባር ተኮር ግለሰብ መሆኑን ስለሚያውቅ እና ያዘጋጀው ጸሑፍ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብሎ ስለገመተ፣ በጥሞና አነበበው፤ ጽሑፉም ጠቀሜታ እንዳለው እርግጠኛ ሆነ። ከዚያም ረቂቁን ጉዳዩ ያገባቸዋል ብሎ የገመታቸውን ሁለት ወዳጆቹን (ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነና ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ) እንዲያነቡትና አስተያየታቸውን እንዲያካፍሉት ጠየቃቸው። እነሱም ፈቃደኝነታቸውን ከገለጡለት በኋላ ጊዜ ሳይፈጁ፣ ከሁለት ሺሕ ሁለት መቶ በላይ ገጾች የነበረውን ረቂቅ አንብበው፣ ጽሑፉ ቢታተተም ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመኑ። የመጽሐፉን ረቂቅ ፈትሾ፣ አስገምግሞ፣ ሊያሳትመው ይችል ይሆናል ብለው በማሰብም፤ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አካል የሆነው ለ”ኢትዮጵያ ሳይንስ ፕሬስ” ረቂቁን አስገቡ።
በዚያን ወቅት የ”ኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ” አማካሪ ቦርድ አልተሠየመለትም ነበር። ስለሆነም በአካዳሚው የሥራ አስፈጻሚ ዲሬክተር በፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ ጥያቄ አንድ ኮሚቴ ተቋቋመ። የኮሚቴውም አባላት ራሱ ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ የኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ አባል፣ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ አባል እና አቶ ብርሃኑ ደቦጭ የኮሚቴው ጸሐፊ ሆነው ተሠየሙ።
ይኽንኑ ሰነድ፣ ማለትም በብርሃኑ ባይህ እንግዳ፤ “ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞና የኢትዮጵያ አብዮት” በሚል ርእስ የተጻፈውን ከሁለት ሺሕ ሁለት መቶ በላይ ገጾች ያሉትን ረቂቅ ጽሑፍ በየግላቸው አንብበው አስተያየታቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ፤ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ፣ አቶ ብርሃኑ ደቦጭ (በወቅቱ የፕሬሱ ሐላፊ) እና ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ተጠየቁ። ሦስቱም ፈቃደኞች ሆነው ጽሑፉን ከአነበቡ በኋላ፤ በአጭሩ የረቂቁ ጠቃሚነት የማያጠያይቅ መሆኑን እና ቢታተም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው በመግለጽ ተመሳሳይ አስተያየቶች አቀረቡ።
ከአስተያየቶቹ ለመጥቀስ ያህል፤ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ (የታሪክ ምሁር) ያቀረበው እነሆ፤ “….ይህንን የመሰለ ትልቅ ሥራ አይቼ አስተያየት እንድሰጥ ዕድሉን አካዳሚው ስለቸረኝ አመሰግናለሁ። ።… ይህ ጽሑፍ፡- ያለምንም ጥርጣሬ አፍ ሞልቶ፣ እጅግ ጠቃሚ የሆነ ጸሑፍ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ምክንያቱም እስከ አሁን የማናውቃቸውን ብዙ ነገሮች ስለሚያሳውቀን እና ከዚህ በፊት የምናውቃቸው ጉዳዮች ከሆኑም ስለሚያጠናክራቸው፣ ወይም ስለሚቃረናቸው ነው።
መጽሐፉን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። ክፍል አንድ እስከ ደርግ መቋቋም ድረስ ያለው የጸሐፊው ትውስታ ሲሆን፣ ክፍል ሁለት የደርግ ዘመን ይሆናል። ሁለቱም ዋጋ አላቸው። ሁለቱም ክፍሎች ታሪክ ለሚያጠናው አንባቢም ሆነ፣ ለታሪክ ተመራማሪው ብዙ መረጃ ይሰጣሉ። የመጀመሪያው ክፍል ማለትም ቅድመ ደርግ ክፍል ለሁለተኛው ክፍል ታሪካዊ ዐውዱን (historical context) ይሰጠዋል። በዚህ የተነሣ ኋላ ላይ ትላልቅ የፖለቲካ ወይም ወታደራዊ ሥልጣን ይዘው በሀገር ደረጃ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ግለሰቦችን በወጣትነታቸው እናገኝበታለን፡- ጌታቸው ናደው፣ ደምሴ ቡልቶ፣ ተፈሪ ተክለ ሃይማኖት፣ ወዘተ…፤ ከጀነራሎችንም ቢሆን አንዳንዶቹን ቀድመን እንተዋወቃቸዋለን፡-ጀኔራል አማን፣ ጀኔራል ነጋ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ስለዚህ የመጀመሪያው እና የሁለተኛው ክፍል አንድ አምሳል ናቸው ማለት ይቻላል። የዚህ ትውስታ ትልቅ አስተዋጽዖ በስፋት መቅረቡ፣ ብዙ ጉዳዮችን በዝርዝር ማየቱ ነው። በዚህ የተነሣ እጅግ ብዙ ቁም ነገሮች ተዳስሰውበታል። እሰከ አሁን ከታተሙት የትዝታ መጻሕፍት ጋር፡- ማለት ከመንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ከፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ እና ከፍስሐ ደስታ ሥራዎች ጋር ሲወዳደር ይኸኛው በሚያቀርበው ዝርዝር ምክንያት ልቆ ይገኛል።… አሁን አስረግጬ ማቅረብ የምፈልገው ሐሳብ ይህ ሥራ እጅግ ጠቃሚ እና ቋሚ መጽሐፍ መሆኑን ነው። ለዚህም ለጸሐፊው ያለኝን ከፍተኛ አድናቆት መግለጽ እወዳለሁ። ጽሑፉ ገና ለኅተመት አልደረሰም፣ ሰፊ የአርትዖት ሥራ ይቀረዋል። ………..ይህን ሁሉ ካልኩ በኋላ የሚከተለውን ሐሳብ አቀርባለሁ።
1ኛ) ጽሑፉ ቶሎ ተዘጋጅቶ ቢታተም ይመረጣል። «ቶሎ» ስል ከስድስት ወር እስከ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ማለቴ ነው።
2ኛ) ጽሑፉን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ቢያሳትመው ጥራት ባለው መልክ ይሠራዋል ብዬ አምናለሁ። ሥራውም የተፋጠነ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ……..።
ከዚያም በአካዳሚው ፕሬስ እንዲታተም ተወሰነ። ከደራሲው ከኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እንግዳ መጽሐፉ በአካዳሚው ፕሬስ አንዲታተም በጸሑፍ (የእጅ ጽሑፍ ማስረጃ) ለአካዳሚው ፈቃድ ተሰጠ።እንዲሁም ጽሑፉ (ረቂቁ) እንዳለ፣ ሳይነካካ፣ ለተመራማሪዎች የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለገል፣አንድ ቅጅ በኢትዮጲያ ጥናት ኢንስቲቲዩት ቤተ መጻሕፍት፣ ሁለተኛው ቅጅ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ቤተ መጻሕፍት እንዲቀመጥ ተወሰነ። የጽሑፉ ገጾች ብዙ ስለሆኑ የግድ በሰባት ጥራዞች መከፋፈል አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ። ስለሆነም ሰባት በጠንካራ ሽፋን የተጠረዙ የሰነዱ ረቂቅ ሙሉ ቅጅዎች፤ አንደኛው በኢትዮጲያ ጥናት ኢንስቲቲዩት ቤተ መጻሕፍት ሁለተኛው የሰነዱ ረቂቅ ሙሉ ቅጅ፣ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ቤተ መጻሕፍት እንዲቀመጡ ተደርጓል።
በኅትመት ሂደት የጽሑፉን ገጸ ብዙነት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እንዴት ይታተም ወደሚለው ዝርዘር ተገባ። ለዚህም ተግባር አቶ ብርሃኑ ደቦጭ ያቀረበው ሐሳብ በከፊል አነሆ ” ……. በብርሃኑ ባይህ የተዘጋጀውን ረዢም መጽሐፍ ይዘት በተቻለ መጠን ወደ ሰፊው አንባቢ ለማድረስ እንዲረዳ የተሻለውን ዘዴ ለመጠቆም ነው። ዋነኛው ችግር የመጽሐፉ ረቂቅ ገጽ ብዛት በጣም ብዙ መሆኑ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሁለት አማራጮች አሉ።
አንደኛው ከዚህ መጽሐፍ ውስጥ አንድ በጠቅላላ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር መጽሐፍ ማውጣት መቻሉ ነው። የዚህ አማራጭ ውስንነት ቢያንስ ስለ ሁለት ጉዳዮች ነው።
- አዲሱ መጽሐፍ በሁሉም ጉዳይ ላይ እንዲያተኩር ቢደረግ አሁንም የመጽሐፉን ገጽ ብዛት መጠን መቀነስ እንጂ (የገጹን ብዛት በመጠን) ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ አለመቻሉ፤
- ወደ ተፈለገ መጠን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ከጸሐፊው መነሻ መንፈስ ውጪ ይዘቶችን መቆራረጥን ማስከተሉ፤
- ዋነኛውን ቅጂ በጥናትና ምርምር ቤተ መጻሕፍት ማስቀመጥ ቢቻልም፤ ለብዙ አንባብያን ሊዳረስ አለመቻሉ፤
ሁለተኛው በተለያዩ ተተኳሪ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ከአንድ በላይ መጻሕፍትን ማዘጋጀት ነው። የዚህ አማራጭ ውስንነት ስለ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ይሆናል።
- አሳታሚው በአንድ ጊዜ ሁለት እና ከዚያ በላይ የአንድ ሰው መጻሕፍትን ማሳተሙ አሳማኝነት፣
- በተተኳሪ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑትን መጻሕፍት ለማዘጋጀት የሚያስፈልገው ሥራ እና የሚዘጋጁት መጻሕፍት በየራሳቸው መቆም የሚችሉበትን የአወቃቀርና ማያያዣ በተገቢው ሁኔታ ለመገንባት፤ መጽሐፉን መስመር በመስመር ሙሉ ለሙሉ መረዳትን መሻቱ ናቸው።
ከዚያም ቀጠል አድርጎ “እንደእኔ እንደእኔ ሁለተኛው አማራጭ በሁለት የተለያዩ ምክንያቶች የተሻለ ይመስለኛል።” ይላል።
“መጽሐፉ ቢያንስ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ከጸሐፊው ብቻ የምናገኛቸውን መረጃ ይሰጠናል። እነርሱም፡-
- ስለአብዮቱ ጸሐፊው ያለውን ዕይታ፣ ከአብዮቱ ጋር በተያያዘ በእሱ በኩል የተደረጉ ሁነቶችን፣ አረዳዶችንና ምልከታዎችን መስጠቱ፤
- በወታደራዊው አስተዳደር ሥርዓት ስለ ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ የሚሰጠው መረጃ ነው።
አሳታሚው በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑትን ሁለቱንም መጻሕፍት ሊያሳትም ቢወድ እሰየው፤ ካልሆነም የተመረጠው አንዱን አሳትሞ የቀረው ራሱን የቻለ ስለሆነ በሌላ አሳታሚ ማሳተም ስለሚቻል።
ይህ ከሆነ መጽሐፉ በሦስት ርእሰ ጉዳዮች /ጭብጥ ሊዘጋጅ ይችላል (ቅደም ተከተሉ ታስቦበት ነው)። አንደኛ ስለ አብዮቱ ፤ ሁለተኛ በውጭ ግንኙነት፣ የኤርትራና የሶማሊያ አካባቢ ጉዳዮች፤ ሦስተኛ ስለባለታሪኩ ዕድገት፣ ሙያ፣ የሕይወት ገጠመኝና ዕጣ ፈንታ ናቸው። ……። በጣም የተወሰኑ ቦታ አንዱ ከአንዱ የሚወራረስ ነገር ሊኖረው ይችላል።”
እንግዲህ ይህን መነሻ በማድረግ ነው ረቂቁ በሳይንስ ኣካዳሚ ፕሬስ እንዲታተም የታቀደ። ከዚህ በኋላ፣ የአካዳሚው ፕሬስ የመጀመሪያውን መጽሐፍ ለኅትመት ለማዘጋጀት እንደ ጀመረ፣ የዚህ ተግባር ሐላፊነት ተሰጥቶት የነበረው የአካዳሚው ፕሬስ ሐላፊ አካዳሚውን ተሰናብቶ፣ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ለመከታተል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባ። በዚህ ምክንያት የኅትመት ዝግጅት ተግባር ለወራት ተጓጎለ። ከወራት በኋላ አዲስ የፕሬሱ ሐላፊ ሲሠየምም እሱም የተደራረበ አጣዳፊ ሥራ ስለገጠመው መጽሐፉን ለኅትመት የማዘጋጀቱ ተግባር እንደገና ለመዘግየት ተዳረገ።
ይህ በዚህ እንዳለ “የሳይንስ አካዳሚ ፕሬስ ቦርድ” ስለ ተቋቋመ፣ ቦርዱ ጸሑፉን የተደነገገውን አዲስ ሥርዓት ተከትሎ ማስገምገም ነበረበት። ይህም ተጨማሪ ግማሽ ዓመት ገደማ ፈጀ። አዲሱን ሥርዓት ተከትሎ የተስተናገደውም ግምገማ፣ የረቂቅ ጸሑፉን ጠቃሚነት ስለአበሠረ፣ የሳይንስ አካዳሚ ቦርድ ጽሑፉን ለማሳተም ወሰነ። ስለሆነም የኅትመቱ ሂደት በአዲስ መልክ ተጀመረ።
አሁንም እንደገና ጹሑፉ መጠነ ብዙነቱ ግዙፍ የኅትመት ችግር ሆኖ ተገኘ። ብዙ አማራጮች ከተፈተሹ በኋላ የተመረጠው መፍትሔ ሰነዱን ሁለት የተለያዩ መጽሐፎች አድርጎ ማዘጋጀት እንዲሆን ተወሰነ። ውሳኔውም አንደኛው የሕይወት ታሪኩን የያዘ ሲሆን፤ ያም ዕድገቱን እንዲሁም ቅደመ ደርግ ውትድርና ዘመኑን “ዕድገቴ እና ወታደራዊ ሕይወቴ” በሚል ርእስ፤ ሁለተኛው የደርግ አባል ሆኖ ከተመረጠ በኋላ፣ በደርግ ዘመን የነበረውን የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያስተናገድ “የኢትዮጵያ አብዮትና ተሳትፎዬ” በሚል ርእስ ለአንባብያን ማቅረብ ነበር።
ረቂቁ የግድ ማጠር ስለነበረበት፣ አልፎ አልፎ እንዲያጥር ተደርጓል፡፡ ያ ሲደረግ፣ ያጠረው ጽሑፍ ተለይቶ እንዲታወቅ በአይታሊክስ ቀርቧል፡፡
ሌላው ከፍተኛ ተግዳሮት የረቂቁ ተነባቢነት ነበር። ረቂቁ የተዘጋጀው እንደ ቀን ተቀን ድርጊት ሆኖ ነበር ። ጽሑፉን ወጥ እና ተነባቢ ለማድረግ የግድ ትረካዎችን ከቦታ ቦታ ማንሸራሸር አስፈልጓል። በተጨማሪ ረቂቁ ምንም እንኳን በምዕራፎች ቢከፋፈልም፣ እያንዳንዱ ምዕራፍ ርእስ አልነበረውም። የተለያዩ ትረካዎች በአንድ ምዕራፍ ውስጥ፣ ምንም መከፋፋያ ርእስ እና ንኡስ ርእስ ሳይሰጣቸው ነበር የተተረኩት። ስለሆነም ጽሑፉ ትርጉም ይሰጣል ተብሎ በተገመተበት መንገድ ለምዕራፎቹ ርእስ ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም ትረካው ወጥ ሆኖ ለንባብ እንዲያመች ለማድረግ፣ እያንዳንዱ ምዕራፍ በንኡስ ርእሶች ተከፋፍሏል። ይህ ሁሉ ሲደረግ ከደራሲው ጋር በመመካከረና ፈቃድ በማግኘት ነበር። መጽሐፉን በሁለት ክፍሎች ማቅረቡ ስለታመነበት፣ ለንባብ እንዲያመች፣ ሁለት ክፍሎች ያሉት አንድ መጽሐፍ ሆኖ እንዲወጣ ተወሰነ፡፡ ክፍል አንድ የሕይወት ታሪኩን አጠር ባለ መልክ ያካተተ ሲሆን፤ ክፍል ሁለት ብርሃኑ ባይህ በደርግ አባልነቱ የነበረውን የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያካትት ነው፡፡ ለምዕራፎቹ ርእስ መስጠትም ሆነ፣ በምዕራፎች ውስጥ ያሉ ርእሶችን ማዘጋጀት፣ ብሎም ጽሑፉን ማሳጠር እና መጽሐፉን በሁለት ክፍሎች የማዘጋጀቱ ተግባር የተሰጠው ለፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ነበር፡፡ ዋናው ምክንያት ደራሲውን በፈለገው ጊዜ ማግኘት የሚችለው እሱ ስለሆነ ነበር፡፡