የክረምት የሥነ ጽሑፍ ሥልጠና እየተሰጠ ነው

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ትብብር 50 ለሚሆኑ ወጣቶች የሥነ ጽሑፍ ሥልጠና መሰጠት ጀምሯል፡፡

በክረምቱ ለ2 ወር የሚቆይ ሥልጠና በመስጠት የሥነ ጽሑፍ ግንዛቤን ለማሳደግ፣ አንባብያን እና ጸሐፊያንን ለማፍራት እንደታሰበ የሥልጠናው አስተባባሪዎች አቶ ገዛኸኝ ሀብቴ እና አቶ ይታገሱ ጌትነት (ከደራሲያን ማኅበር) አሳውቀዋል፡፡

ሥልጠናው በሳምንት አምስት ቀን በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ድርጅት (ወመዘክር) ግቢ በሥነ ግጥም፣ አጫጭርና ረጅም ልበ-ወለዶች፣ ሂስና ሂሳዊ ንባብ፣ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ እና ፎክሎር ላይ በማተኮር እንደሚሠጥም ታውቋል፡፡ በተያያዥነት ለተከታታይ 8 ሳምንታት ዘወትር ቅዳሜ ደግሞ በትርጉም ሥራ፣ የፊልምና ቴአትር ጥበብ፣ ፍልስፍናና ሥነ ጽሑፍ፣ ሙዚቃና ሥነ ጽሑፍ እንዲሁም የግዕዝ መግቢያ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር በሚገኘው በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል ይካሄዳል፡፡

አንጋፋ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎችን በሥልጠናዎቹ ላይ በመጋበዝ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ለማድረግም ታቅዶ እየተሠራ እንደሆነ አስተባባሪዎቹ ገልፀዋል፡፡