ባዮቴክኖሎጂያዊ የፍሳሽ ውሃ ሕክምና ሂደት

የፍሳሽ ውሃን ማስወገድና ማጣራት መቼ ተጀመረ?

የፍሳሽ ውሃን የማስወገድ ሥራ በታሪክ ከ4000 ዓመተ-ዓለም ጀምሮ በባቢሎናውያን ይተገበር እንደነበር የሚያሳዩ በአርኬዎሎጂያዊ ጥናት የተገኙ የተለያዩ ቅሪተ-አካል መገኘታቸውን የጠቆሙት የገለጻው አቅራቢ ዶ/ር አደይ ፈለቀ፣ ኋላም ከ3000-500 ዓመተ-ዓለም ድረስ በግሪክ፣ ቱርክ (ኤፌሶን) እና ሮማውያን በቤት ውስጥ የሚገኝ ፍሳሽ ውሃን በተሻሻለ መንገድ ማስወገድ የተለመደ እየሆነ እንደመጣ ገልጸዋል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላም በቱርክ ከቤት ውስጥ የሚወገድ ፍሳሽ ሌላ አካባቢያዊ ችግር እንዳይፈጥር በቦይ አድርጎ በማፋሰስ ከመኖሪያ አካባቢ እርቆ እንዲወገድ የሚያስችላቸውን ዘዴ ይጠቀሙ እንደነበር ዶ/ር አደይ አጀማመሩን እና ሂደቱን አብራርተዋል፡፡

በአውሮፓም ዘግየት ብሎም ቢሆን በመካከለኛው ዘመን፣ እንዲሁም በ19ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን መባቻ አካባቢ ወደ ወንዞች የሚገባን የአካባቢና የኢንዱስትሪ ፍሳሽ ውሃ በኅብረተሰቡ ላይ የሚያመጣውን የጤና ችግር (ከጉድጓድ የሚገኝ የመጠጥ ውሃን በመበከሉ) መገንዘብ ተችሏል፡፡ በዚህም እ.አ.አ በ1868 በለንደን Abbey Mills Pumping Station – The Sewage Cathedral የተሰኘ የፍሳሽ ውሃ ማሰባሰቢያና ወደሚወገድበት ቦታ በግፊት ኃይል ማጓጓዣ ጣቢያ ተመሠረተ፡፡ እ.አ.አ በ1874 ደግሞ በተሻሻለ መንገድ በእንግሊዟ ብራይተን የፍሳሽ ውሃ ማሰባበሲያ ጣቢያ ተሠርቶ ለአገልግሎት በቅቷል፡፡

ነገር ግን መዳረሻው ላይ የሚከማቸው ፍሳሽ ምን መደረግ እንዳለበት ማወቁ ሌላው የምርምሮች የትኩረት አካል ሆነ፡፡

በሂደትም አካባቢንም ሆነ የሠው ልጆችን ጤና እንዳይጎዳ ማጣራት አስፈላጊ እንደሆነ በመታመኑ፣ ኬሚካሎችንና የሸክላ ስብርባሪን በመጠቀም እ.አ.አ ከ1856-1876 ድረስ 400 የሚሆኑ የማጣሪያ ዘዴ የፈጠራ ሥራዎች ተመዝግበዋል፡፡ በ1890 በታላቋ ብሪታኒያ ብቻ 200 የሚደርሱ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ  የማጣሪያ ጣቢያዎች ተገንብተዋል፡፡

በዚህም ሂደት ውስጥ የኬሚካል ማጣሪያ ሥራው ወጪ በማብዛቱና ሌላ አይነት የብክለት ችግር በመፍጠሩ፣ አዲስ የማጣሪያ መንገድ አስፈልጎ ነበር፡፡ በዚህም ደቂቅ-ዘአካላትን (micro-organisms) በማሳተፍ ባዮቴክኖሎጂያዊ የፍሳሽ ውሃ ሕክምና ሂደት እ.አ.አ ከ1914 – 1970 እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ደቂቅ-ዘአካላት በካይ የሆኑ ንጥረ-ነገሮችን እንዲመገቡ በማድረግ ማስወገድ ቀላልና አዋጭ መንገድ በመሆን እየተለመደና በስፋት ሥራ ላይ እየዋለ የመጣ ሂደት ነው፡፡

የገለፃውን ቪዲዮውን እዚህ ላይ በመጫን ይመልከቱ